ከፍተኛ የህወሓት አመራሮች አዲስ አበባ ውስጥ ፍርድ ቤት ቀረቡ

አቶ ስብሐት ነጋ፣ ወ/ሮ ኬሪያ ኢብራሂም፣ አቶ አባይ ወልዱ እና ወ/ሮ ቅዱሳን ነጋ
ባለፈው ሳምንት ትግራይ ውስጥ ተይዘው ወደ አዲስ አበባ ከተወሰዱት ከፍተኛ የህወሓት አመራሮች መካከል አቶ ስብሐት ነጋንና ወ/ሮ ኬሪያ ኢብራሂምን ጨምሮ በርካታ ግለሰቦች ዛሬ አርብ ፍርድ ቤት ቀረቡ።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደዘገበው ፍርድ ቤት የቀረቡት ሰዎች ሁለቱን ግለሰቦች ጨምሮ በትግራይ ውስጥ ከተከሰተው ቀውስ ጋር በተያያዘ ወንጀል የተጠረጠሩ 20 የህወሓት አመራሮች ናቸው።
ግለሰቦቹ አዲስ አበባ ውስጥ በሚገኘው የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ችሎት የቀረቡ ሲሆን፤ ከእነዚህም መካከል የህወሓት ቀደምትና ከፍተኛ አመራሮች የነበሩት አቶ ስብሃት ነጋ፣ አቶ አባይ ወልዱ፣ ወ/ሮ ኬሪያ ኢብራሂም፣ አብርሃም ተከስተ (ዶ/ር)፣ ወይዘሮ ቅዱሳን ነጋ፣ ወ/ሮ ሙሉ ሙሉ ገብረእግዚአብሔር እና አቶ አባዲ ዘሞ እንደሚገኙበት ተገልጿል።
ተጠርጣሪዎቹ በዋናነት ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን በኃይል ለመናድ ሕገ ወጥ ቡድን አደራጅተው በሰሜን ዕዝ ላይ ጥቃት እንዲፈጸም በማድረግ፣ ወጣቶች ለጦርነት እንዲዘምቱ በመቀስቀስ፣ የነዳጅ ማከማቻዎች እንዲዘረፉ በማድረግ፣ የበርካታ የመከላከያ ሠራዊቱ አባላት ህይወት እንዲጠፋ አድርገዋል በሚል መከሰሳቸውን የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ዘግቧል።
በተጨማሪም በሕግ ባልተሰጣቸው ስልጣን ከተለያዩ አገራት ጋር ግንኙነት በመፍጠር፣ ለጦርነት ገንዘብ መሰብሰብ፣ በጎንደርና በባሕር ዳር ከተሞች ውስጥ በሚገኙ አውሮፕላን ማረፊያዎች ላይ ሮኬት እንዲተኮስና የንጹሃን ህይወት እንዲጠፋ በማስደረግ እና በሌሎች ወንጀሎች መሳተፋቸውን የፌደራል ፖሊስ የወንጀል ምርመራ ቡድን ለፍርድ ቤቱ አስረድቷል።
እነዚህ ከፍተኛ የህወሓት አመራሮች በፖሊስ የቀረቡባቸውን የወንጀል ክሶች በሙሉ አልፈጸምንም ብለው ጉዳያቸውን ላደመጠው የፌደራል ፍርድ ቤት መግለጻቸው ተነግሯል።
ፍርድ ቤት ጉዳያቸውን ከሰማው 20 ሰዎች መካከል የቀድሞው የትግራይ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አባይ ወልዱና የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባና የከተማዋ ትራንስፖርት ቢሮ ኃላፊ የነበሩት ሰለሞን ኪዳኔ (ዶ/ር) ህክምና ላይ በመሆናቸው በችሎቱ አለመገኘታቸው ተነግሯል።
ጉዳዩን እየመረመረ ያለው መርማሪ ፖሊስ ፍርድ ቤት በቀረቡት 20 ተጠርጣሪዎች ላይ የ14 ቀናት ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ጠይቆ ተፈቅዶለታል።
በዕለቱ የፍርድ ቤት ውሎ መቅረባቸው በስም ከተጠቀሰው ቁልፍ የህወሓት አመራሮች በተጨማሪ የሌሎቹ ተጠርጣሪዎች እነማን እንደሆኑ በኢዜአ ዘገባ ላይ አልገለጸም።
ጥቅምት 24/2013 ዓ.ም የህወሓት ኃይሎች በሰሜን ዕዝ ላይ ጥቃት ፈፅመዋል መባሉን ተከትሎ በትግራይ ክልል ወታደራዊ ግጭት ተቀስቅሶ ክልሉን ይመራ የነበረው ሕወሓት ከሥልጣን ከተወገደ በኋላ የተለያዩ የቡድኑ አመራሮች እየተፈለጉ ይገኛሉ።
በትግራይ ክልል ከተከሰተው ቀውስ ጋር በተያያዘ የፌደራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግና የፌደራል ፖሊስ በበርካታ የህወሓት ወታደራዊና ፖለቲካዊ አመራሮች ላይ የእስር ትዕዛዝ ማውጣታቸው ይፋ ማድረጋቸው ይታወሳል።
ለእስር ማዘዣውም ዋነኛ ምክንያቶቹ ህወሓትን በበላይነት በመምራት፣ በትግራይ ክልል በሚገኘው በአገር መከላከያ ሠራዊት የሰሜን ዕዝ ላይ ጥቃት በመፈፀም፣ የአገር ክህደት ወንጀል ፈጽመዋል፣ የመከላከያ ሠራዊትና የፖሊስ አባላት እንዲታገቱ አድርገዋል በሚል ተጠርጥረው መሆኑንም መንግሥት ገልጿል።
በተጨማሪም የቀድሞው የአገሪቱ ጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም የነበሩት ሜጀር ጄኔራል ጻድቃን ገብረተንሳይን ጨምሮ፣ ከፍተኛ የቀድሞ የኢትዮጵያ አየር ኃይል፣ የመከላከያ ሠራዊትና የፖሊስ አመራሮችም በአገር ክህደትና በሠራዊት አባላት ላይ ወንጀል ፈፅመዋል በሚል ተጠርጥረው የመያዣ ትዕዛዝ ወጥቶባቸዋል።
ዛሬ ፍርድ ቤት ከቀረቡት የህወሓት ከፍተኛ አመራሮች መካከል የ86 ዓመቱ አዛውንት አቶ ስብሐት ነጋ፣ ቀደምት የሕወሓት መሪና በሕወሓት/ኢህአዴግ ውስጥ ከፍተኛ ተሰሚነት የነበራቸው እንዲሁም ኤፈርት የተባለውን የድርጅቱን ግዙፍ የምርትና የአገልግሎት ተቋም በበላይነት ሲመሩ የቆዩና በመጨረሻም የኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት ስትራተጂያዊ ጥናት ተቋምን ዋና ዳይሬክተር የነበሩ ናቸው።
ወ/ሮ ኬሪያ ኢብራሂም የቀድሞ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈጉባኤ የነበሩ ሲሆን በፌደራል መንግሥቱና በህወሓት መካከል የነበረው ውዝግብ ተካሮ ወደ ወታደራዊ ግጭት ከመግባታቸው ከጥቂት ወራት በፊት ስልጣናቸውን ለቀው ወደ ትግራይ ያቀኑ ሲሆን፤ በቀዳሚነት እጃቸውን መስጠታቸው ይታወሳል።
ወ/ሮ ሙሉ ገብረ እግዚአብሔር ደግሞ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባልና የትራንስፖርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዲኤታ ሆነው ሰርተዋል።
አባይ ወልዱ ደግሞ የሕወሓት ቀደምት ታጋይ የነበሩና በህወሓት ውስጥ በተለያዩ የኃላፊነት ደረጃዎች ቆይተው የትግራይ ክልል ርዕሰ መስተዳደር ሆነው ሰርተዋል።
አብርሃም ተከስተ (ዶ/ር) ደግሞ በ2010 በአገሪቱ ውስጥ እስከተካሄደው ለውጥ ድረስ የአገሪቱ የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስትር ዲኤታ የነበሩ ሲሆን፤ ባለፉት ሁለት ዓመታት ወደ ትግራይ ሄደው የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳደርና የፋይናንስና ኢኮኖሚ ልማት ቢሮ ኃላፊ ነበሩ።
የአቶ ስብሐት ነጋ ታናሽ እህት የሆኑት ወይዘሮ ቅዱሳን ነጋ ከቀደምት የህወሓት ሴት ታጋዮች መካከል አንዷ የነበሩ ሲሆን የፓርቲው ማዕከላዊና ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል፣ የመቀለ ከንቲባ እና የትግራይ ክልል ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ሆነው ለበርካታ ዓመታት ሰርተዋል።
ዛሬ ፍርድ ቤት ቀርበዋል ከተባሉት ግለሰቦች በተጨማሪ በርካታ የህወሓት ወታደራዊና ፖለቲካዊ አመራሮች በቁጥጥር ሰር የዋሉ ሲሆን ጥቂት የማይባሉት መገደላቸውን የመከላከያ ሠራዊት መግለጹ ይታወሳል።
የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት እየተፈለጉ ያሉትን የሕወሓት ከፍተኛ አመራሮችን ጠቁሞ በመንግሥት ቁጥጥር ስር እንዲውሉ የሚያስችል መረጃዎችን ለሚሰጡ ሰዎች የአስር ሚሊዮን ብር ሽልማት እንደሚሰጥ ቃል መግባቱ ይታወሳል።
No comments:
Post a Comment